ኦሪት ዘፍጥረት1-2
መጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ።
2 ፤ ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር።
3 ፤ እግዚአብሔርም። ብርሃን ይሁን ኣለ፤ ብርሃንም ሆነ።
4 ፤ እግዚአብሔርም ብርሃኑ መልካም እንደ ሆነ አየ፤ እግዚብሔርም ብርሃንንና ጨለማን ለየ።
5 ፤ እግዚአብሔርም ብርሃኑን ቀን ብሎ ጠራው፥ ጨለማውንም ሌሊት አለው። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አንድ ቀን።
6 ፤ እግዚአብሔርም። በውኆች መካከል ጠፈር ይሁን፥ በውኃና በውኃ መካከልም ይክፈል አለ።
7 ፤ እግዚአብሔርም ጠፈርን አደረገ፥ ከጠፈር በታችና ከጠፈር በላይ ያሉትንም ውኆች ለየ፤ እንዲሁም ሆነ።
8 ፤ እግዚአብሔር ጠፈርን ሰማይ ብሎ ጠራው። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ሁለተኛ ቀን።
9 ፤ እግዚአብሔርም። ከሰማይ በታች ያለው ውኃ በአንድ ስፍራ ይሰብሰብ፥ የብሱም ይገለጥ አለ እንዲሁም ሆነ።
10 ፤ እግዚአብሔርም የብሱን ምድር ብሎ ጠራው፤ የውኃ መከማቻውንም ባሕር አለው፤ እግዚእብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።
11 ፤ እግዚአብሔርም። ምድር ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን በምድርም ላይ እንደ ወገኑ ዘሩ ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን ታብቅል አለ፤ እንዲሁም ሆነ።
12 ፤ ምድርም ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን እንደ ወገኑ ዘሩም ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን እንደ ወገኑ አበቀለች። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።
13 ፤ ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ሦስተኛ ቀን።
14 ፤ እግዚአብሔርም አለ። ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ፤ ለምልክቶች ለዘመኖች ለዕለታት ለዓመታትም ይሁኑ፤
15 ፤ በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር ብርሃናት ይሁኑ፤ እንዲሁም ሆነ።
16 ፤ እግዚአብሔርም ሁለት ታላላቆች ብርሃናትን አደረገ፤ ትልቁ ብርሃን በቀን እንዲሠለጥን፥ ትንሹም ብርሃን በሌሊት እንዲሰለጥን፤ ከዋክብትንም ደግሞ አደረገ።
17 ፤ እግዚአብሔርም በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር አኖራቸው፤
18 ፤ በቀንም በሌሊትም እንዲሠለጥኑ፥ ብርሃንንና ጨለማንም እንዲለዩ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።
19 ፤ ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አራተኛ ቀን።
20 ፤ እግዚአብሔርም አለ። ውኃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾች ታስገኝ፥ ወፎችም ከምድር በላይ ከሰማይ ጠፈር በታች ይብረሩ።
21 ፤ እግዚአብሔርም ታላላቆች አንበሪዎችን፥ ውኃይቱ እንደ ወገኑ ያስገኘቻቸውንም ተንቀሳቃሾቹን ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ፥ እንደ ወገኑ የሚበሩትንም ወፎች ሁሉ ፈጠረ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።
22 ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ባረካቸው። ብዙ ተባዙም የባሕርንም ውኃ ሙሉአት፤ ወፎችም በምድር ላይ ይብዙ።
23 ፤ ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አምስተኛ ቀን።
24 ፤ እግዚአብሔርም አለ። ምድር ሕያዋን ፍጥረታትን እንደ ወገኑ፥ እንስሳትንና ተንቀሳቃሾችን የምድር አራዊትንም እንደ ወገኑ፥ ታውጣ፤ እንዲሁም ሆነ።
25 ፤ እግዚአብሔር የምድር አራዊትን እንደ ወገኑ አደረገ፥ እንስሳውንም እንደ ወገኑ፥ የመሬት ተንቀሳቃሾችንም እንደ ወገኑ አደረገ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።
26 ፤ እግዚአብሔርም አለ። ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ።
27 ፤ እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።
28 ፤ እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው። ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።
29 ፤ እግዚአብሔርም አለ። እነሆ መብል ይሆናችሁ ዘንድ በምድር ፊት ሁሉ ላይ ዘሩ በእርሱ ያለውን ሐመልማል ሁሉ፥ የዛፍን ፍሬ የሚያፈራውንና ዘር ያለውንም ዛፍ ሁሉ ሰጠኋችሁ፤
30 ፤ ለምድርም አራዊት ሁሉ፥ ለሰማይም ወፎች ሁሉ፥ ሕያው ነፍስ ላላቸው ለምድር ተንቀሳቃሾችም ሁሉ የሚበቅለው ሐመልማል ሁሉ መብል ይሁንላቸው፤ እንዲሁም ሆነ።
31 ፤ እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ስድስተኛ ቀን።
ማይና ምድር ሠራዊታቸውም ሁሉ ተፈጸሙ።
2 ፤ እግዚአብሔርም የሠራውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ፈጸመ፤ በሰባተኛውም ቀን ከሠራው ሥራ ሁሉ ዐረፈ።
3 ፤ እግዚአብሔርም ሰባተኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም፤ እግዚአብሔር ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሱ ዐርፎአልና።
4 ፤ እግዚአብሔር አምላክ ሰማይንና ምድርን ባደረገ አምላክ ሰማይንና ምድርን ቀን፥ በተፈጠሩ ጊዜ የሰማይና የምድር ልደት ይህ ነው።
5 ፤ የሜዳ ቁጥቋጦ ሁሉ በምድር ላይ ገና አልነበረም፤ የሜዳውም ቡቃያ ሁሉ ገና አልበቀለም ነበር፤ እግዚአብሔር አምላክ ምድር ላይ አላዘነበም ነበርና፥ ምድርንም የሚሠራባት ሰው አልነበረም፤
6 ፤ ነገር ግን ጉም ከምድር ትወጣ ነበር፥ የምድርንም ፊት ሁሉ ታጠጣ ነበር።
7 ፤ እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ።
8 ፤ እግዚአብሔር አምላክም በምሥራቅ በዔድን ገነትን ተከለ የፈጠረውንም ሰው ከዚያው አኖረው።
9 ፤ እግዚአብሔር አምላክም ለማየት ደስ የሚያሰኘውን፥ ለመብላትም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከምድር አበቀለ፤ በገነትም መካከል የሕይወትን ዛፍ፥ መልካምንና ክፉን የሚያስታውቀውንም ዛፍ አበቀለ።
10 ፤ ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ ከዔድን ይወጣ ነበር፤ ከዚያም ለአራት ክፍል ይከፈል ነበር።
11 ፤ የአንደኛው ወንዝ ስም ፊሶን ነው፤ እርሱም ወርቅ የሚገኝበትን የኤውላጥ ምድርን ይከብባል፤ የዚያም ምድር ወርቅ ጥሩ ነው፤
12 ፤ ከዚያም ሉልና የከበረ ድንጋይ ይገኛል።
13 ፤ የሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው፤ እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል።
14 ፤ የሦስተኛውም ወንዝ ስም ጤግሮስ ነው፤ እርሱም በአሦር ምሥራቅ የሚሄድ ነው።
15 ፤ አራተኛውም ወንዝ ኤፍራጥስ ነው። እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በዔድን ገነት አኖረው።
16 ፤ እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው። ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤
17 ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።
18 ፤ እግዚአብሔር አምላክም አለ። ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት።
19 ፤ እግዚአብሔር አምላክም የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ሁሉ ከመሬት አደረገ፤ በምን ስም እንደሚጠራቸውም ያይ ዘንድ ወደ አዳም አመጣቸው፤ አዳምም ሕያው ነፍስ ላለው ሁሉ በስሙ እንደ ጠራው ስሙ ያው ሆነ።
20 ፤ አዳምም ለእንስሳት ሁሉ፥ ለሰማይ ወፎችም ሁሉ፥ ለምድር አራዊትም ሁሉ ስም አወጣላቸው፤ ነገር ግን ለአዳም እንደ እርሱ ያለ ረዳት አልተገኘለትም ነበር።
21 ፤ እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍን ጣለበት፥ አንቀላፋም፤ ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በሥጋ ዘጋው።
22 ፤ እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት።
23 ፤ አዳምም አለ። ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፤ እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል።
24 ፤ ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።
25 ፤ አዳምና ሚስቱ ሁለቱም ዕራቁታቸውን ነበሩ፥ አይተፋፈሩም ነበር።