ውሃ ከሮክ
እስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ እግዚአብሔር እንዳዘዘ ከሲን ምድረ በዳ ሊጓዙ ተነሡ፥ በራፊዲምም ሰፈሩ፤ ሕዝቡም ይጠጡ ዘንድ ውኃ አልነበረም።
2 ፤ ሕዝቡም ሙሴን ተጣሉት። የምንጠጣውን ውኃ ስጠን አሉት። ሙሴም። ለምን ትጣሉኛላችሁ? እግዚአብሔርንስ ለምን ትፈታተናላችሁ? አላቸው።
3 ፤ ሕዝቡም በዚያ ስፍራ ውኃ ተጠሙ። እኛንና ልጆቻችንን ከብቶቻችንንም በጥማት ልትገድል ለምን ከግብፅ አወጣኸን? ሲሉ በሙሴ ላይ አንጐራጐሩ።
4 ፤ ሙሴም። ሊወግሩኝ ቀርበዋልና በዚህ ሕዝብ ምን ላድርግ? ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።
5 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። በሕዝቡ ፊት እለፍ፥ ከእስራኤልም ሽማግሌዎች ከአንተ ጋር ውሰድ፤ ወንዙንም የመታህባትን በትር በእጅህ ይዘሃት ሂድ።
6 ፤ እነሆ እኔ በዚያ በኮሬብ በዓለት ላይ በፊትህ እቆማለሁ፤ ዓለቱንም ትመታለህ፥ ሕዝቡም ይጠጣ ዘንድ ከእርሱ ውኃ ይወጣል አለው። ሙሴም በእስራኤል ሽማግሌዎች ፊት እንዲሁ አደረገ።
7 ፤ ስለ እስራኤልም ልጆች ክርክር። እግዚአብሔር በመካከላችን ነውን ወይስ አይደለም? ሲሉ እግዚአብሔርን ስለተፈታተኑት የዚያን ስፍራ ስም ማሳህ፥ ደግሞም መሪባ ብሎ ጠራው።